The Tigray War 

Witnesses from the Victims

Listen to what the Irob elders displaced in Mekelle say about the war and its impact on their community here 

The Irob People: A Christian Ethnic Minority Caught between the Hammer and the Anvil in  the Tigray War in Ethiopia

Budapest Report 2021_Article_Irob_Etiopia.pdf

Updates on the Impacts of the 2020-2022 Tigray War on Irob Minority

ከመገዳደል ታሪክ ካልወጣን አገርም ፖለቲካም አይኖረንም!

ግርማይ ግዛኸኝ 

መግቢያ

የኢትዮጵያ ታሪክ የመገዳደል ታሪክ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም፣ ማሕበራዊ ለውጥ ማምጣት ሳንችል ቀርተናል። የቀደመውን መገዳደልና ጦርነት ብናወግዝም የባስኑ በግራም በቀኝም ግድያና፣ ፍጅትን በማስተናገድ ላይ ነን። ስብእና ከኛ ርቋል፣ በግድያና ሞት የሚደሰትና የሚጨፍር ትውልድም እያፈራን እንዳይሆን ያሰጋል። ነውር የማናውቅ ግብዞች ሆነናል። ጦርነት አውዳሚ ነው ብሎ መለፍለፍና በተግባር ማሳየት እጅጉን ይለያያሉ። ነገን አሻግረን ከማየት ስሜትና ግለ ግነት ጋርዶናል። ዛሬ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክልሎች የእሳት ራት እየሆኑ ያሉት ንፁሃን ዜጎች ደም ይጮኻል። መጨረሻ ላይም አገራችንን ከባድ ዋጋ ያስከፍላታል። በየአከባቢው በአንዱ ወይም በሌላ ታጣቂ እየተፈጁ ያሉ ንፁሃን ህይወት ያሳዝነኛል ብቻ ሳይሆን እጅጉንም ያስፈራኛል። ምናልባትም በታላቁ መጽሐፍ በብሉይ ኪዳን የሚነገረንን የኖኅ የጥፋት ዝናብና የሶዶምና ጎሞራ ዓይነት በላያችን ላይ እየመጣ ያለውን መዓት ማየት ተስኖን እየደገምነው እንዳይሆንም ያሰጋል። የነዛን ዓይነት ጥፋት እንዲፈጸም የግድ ተመሳሳይ ጥፋት መደረግ አለበት ማለት ላይሆን ይችላል። ክፋት ውስጥ መሆናችንን ግን ማንም የሚነግረን አይደለም። ሁላችንም የየራሳችንን እውነት ይዘናል። ይህ የሚዛናችን መዛባትን ያመላክታል። ዛሬ ወዳጅ የሚባለው ረባም አልረባ የራሴ የሚለውን የሚያምንበትን ሐሳብ የሚሰነዝር ሳይሆን የአንዱን ወይም የሌላውን ሐሳብ ተሸካሚ በመሆኑ የሚያስተጋባ ሆኗል። የተቀረው በግራም በቀኝም ስድብና እርግማን ማስተናገድ ነው። ሆኖም ግን ዕድሜ ለነፃ ሐሳብና ለነፃ ሐሳብ አራማጆች። ይህ ማለት ግን ሁሉም ነፃ ሐሳቦች ጥሩ ናቸው ለማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል!


በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሱ ስላሉ አጸያፊና አስጨናቂ ሰቅጣጭ ግድያዎችና ሞት

ይህ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ከሁሉም በላይ የባሰበትና እጅጉን በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኘው የትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሱ ስላሉ አጸያፊና አስጨናቂ ሰቅጣጭ ግድያዎችና ሞት የተወሰነውን ልበል። 

ትግራይ ውስጥ አስከፊ ጦርነት እየተካሄደ ነው። በዚህ ምክናያትም አሌ የማይባል የንፁሃን ሕይወት እየተቀጠፈ ነው። ስለ ንብረት መውደምና የመንግሥት መዋቅሮች መበጣጠስና አገልግሎቶች መታውክ ማውራት ምቾት ነው። ስለነዚህ ማውራት ጊዜው የሚፈቅደው አይደለም። “በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” እንደሚባለው፣ ይባስ ብሎ በርካታ ለህዝብ ጆሮ የሚደርሱ የተለያዩ በኢትዮጵያዊያን የሚተላለፉ መገናኛ ብዙሃን ስለነዚህ ንፁሃን ሞት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ነው። የተወሰኑ ይህ ፀሓፊ ያልደረሰባቸው ገለልተኛ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት የሚቻል ቢሆንም፣ ከ90% በላይ ግን የአንዱ ወይም የሌላው ደጋፊ ወይም ተለጣፊ በመሆን የሚሰጣቸውን አለዛም በግላቸው የሚጥማቸው ስሜታዊ ዜናዎችና ትንተናዎችን የሚያቀርቡ ሆነው አርፈውታል። ተአማኒ አይደሉም፣ ተሳስተው ህዝብን በማሳሳት ላይ ይገኛሉ። በዚህም ታሪክ ይቅር የማይለው ስሕተት በመፈጸም ላይ ናቸው። በአካል በቦታው ያሉት ያላዩትና ያልሰሙትን ሰምተናል አይተናል እያሉ የሚያወሩ ናቸው። ባጭሩ ምንም አሜነታ የሚጣልባቸው ሊሆኑ አልቻሉም፣ በዚህም አገርና ህዝብን እየጎዱ ነው። አንዱ የሚያወራውን ሌላው በተቃራኒው ያቀርብልናል። በዚህ አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን አለብን። ይኸውም፣ የተኛው እንደሆነ ለጊዜው ሁሉም ላናውቀው የምንችል ቢሆንም፣ ከሁለቱ አንዱ ውሸት መሆኑን ግን በማያሻማ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ምክንያቱም፣ ሁለቱም በአንድ ጊዜና በአንድ ቦታ ሊታዩ አይችሉምና። 

የቶጎጋ የአየር ድብደባን በሚመለከት ሁለት ዓይነት ዜናዎች ይቀርባሉ። በአንድ በኩል በገበያ ዕለት ለገበያ የተሰባሰበውን ገበያተኛ በአየር ተደበደበ የሚል ሲሆን በሌላ በኩል ከመከላከያው ቃል አቀባይ ጀምሮ ሲቪል ሕብረተ ሰብ የተደበደበ የለም፣ የተመታው “የጁንታው” ስብስብ ነው ይላል። በቦታው ነበርን የሚሉ ወገኖች ግን የገበያ ዕለት ለገበያ የተሰበሰበ ሲቪል ዜጋ የሰለባው ገፈት ቀማሽ እንደሆነና ህፃናት ጭምር የድብደባው ሰለባ እንደሆኑ ይገልፃሉ። እነዚህ ወገኖች የታጠቀ ኃይል በገበያው ከህዝብ ጋር ተደባልቆ ይታይ እንደነበረ አላረጋገጡም። ኖረው ቢሆን ኖሮም፣ ለተራው ንፁህ ገበያተኛ ዜጋ ሲባል የአየር ድብደባው መካሄድ እንዳልነበረበት ይህ ፀሐፊ ያምናል። የሆነ ሆኖ ለእነዛንፁሃን መዋቾች ነብስ ምሕረት ለቤተሰቦቻችውም መጽናናትን በመመኘት፣ ቆስለው በህክምና በመረዳት ላይ ላሉትም ፈጣን የማገገሚያ ጊዜ እንዲሆንላቸው ምኞቱን ይገልጻል። ባጠቃላይ ግን ይህንን ዓይነት የወል ጥቃትን አምርሮ ይቃወማል፣ ይኮንናልም። ይህ ዓይነት ጥቃት መራራቅን እንጂ መቀራረብን አያመጣም። እዚህ ላይ ለማስገንዘብ የተፈለገው መገናኛ ብዙኃኖቻችን ከሐላፊነት ይልቅ ለራሳቸው ስሜት ቅድሚያ እንደሚሰጡ ነው። መዲያዎች ተጨባጩን ድርጊት እንዳለ ሊያቀርቡልን ይገባል። ከዛ የራሳቸውን ትንተና ማቅረብ መብታቸው ነው። በቦታውና በጊዜ ያለውን ሁኔታ በራስ ፍላጎት መጥኖ ማቅረብ ግን ተራ ቅጥፈት ከመሆኑም በላይ ሐላፊነትን እንደማጉደል ይቆጠራል። 


በትግራይ ውስጥ እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ግድያ

ሌላው ይህ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ትግራይ ውስጥ እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ግድያን የሚመለከት ነው። የዚህ ግዲያ ፈፃሚ አካል ማን ነው የሚለው ጥያቄ በትክክል ለመመለስ የሚቻል አልሆነም። ሆኖም፣ ግድያው የሚፈጸምባቸው ወገኖች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻል ደረጃ በትግራይ ጊዜአዊ አስተዳደር የተቀጠሩ መሆናቸውና ጄ/ል ፃድቃን በአንድ ቃለ መጠይቃቸው “በልዎም ቀጥቅጥዎም” በሉዋቸው ቀጥቅጧቸው የሚል መልእክት በሳቸው ደረጃ ካለ መሪ የሚጠበቅ ባይሆንም ማስተላለፋቸው፣ በእያንዳንዱ ግድያ ደስታቸውን የሚገልጹ ወገኖች ፖለቲካዊ ውግንና ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሲመዘን፣ ምን እንደሚያመላክት ለአንባቢ የሚተው ጉዳይ ነው። 

እዚህ ላይ ዋና ሊተኲርበት የሚገባ ጉዳይ ግን የዛሬ ግዳዮችን ብቻ ተመልክቶ ዝም ብሎ ማለፍን ነው። ከገዳዩ ጊዜአዊ ደስታ በላይ የሚነድ የቁጣ እሳት በተገዳዩ ቤተ ሰብ እንደሚኖር መጠርጠርም የለበትም። እዛ ውስጥ የሚኖሮው እሳታ እየጋመ የሚሄድ ሳይሆን እየተንከተከተ እንደሚቀጥል ግንዛቤ ማግኘት ይገቧል። በዚህ ምክንያትም ማኅበራዊ ሰላም እየራቀን በቦታው ቅራኔና ቁጭት እያደገ መምጣቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ዓይነት ቅራኔ የተወጠረን ሕብረተ ሰብ መግዛት የሚቻለው በጉልበት ብቻ ይሆናል። ጉልበት ደግሞ ዘላቂ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። መሪዎችም በራስ መተማመን ስለማይኖራቸው ሁሌ የሚያስቡት ራስን መከላከል ስለሚሆን ዜጎችን በእኩል የሚያቅፍ ሥርዓት መገንባት አይችሉም። በዚህ ምክንያትም አገርና ህዝብ ሁሉም ጉድ ፈንድቶ እስኪወጣ ድረስ ሳይተማመኑ አብሮ ይኖሩና መጨራሻ ላይ ሁሉም ፈንድቶ ውንቅጥቅጡ መውጣቱ አይቀሬ ይሆናል። መተማመን አይኖርም። መተማመን ሲጠፋ ምን ሊከሰት እንደሚችል ለማንም መንገር አያስፈልግም። 

ስለሆነም፣ ይህ በማን ይፈጸም በማን ባስቸኳይ መቆም አለበት። በሕገ መንግሥታችን ውስጥ ማንም በህይወት የመኖር መብት እንዳለው ተደንግጓል። ያ የመጣስ መብት የተሰጠው ፍርድ ቤት ብቻ መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት። እያንዳንዱ በራሱ ወይም በቡድን የሚፈጽመው ግድያ ለደርግም አልበጀም። ተገዳዩ ለግዲያ የሚያበቃ ወንጀል ለመፈጸሙ ምንም የሚቀርብ ማስረጃ የለም ብቻ ሳይሆን፣ ቢኖርም እንኳ ያንን ለማስፈጸም በሕግ የቆመ አካል እስከ አላስፈጸመው ድረስ ድርጊቱ ወንጀል ነው። ግድያው አሁን በምናየው ሁኔታ ከቀጠለ ፖለቲካ መሆኑ ቀርቶ የመገዳደያ ሜዳ እንዳንፈጥር እሰጋለሁ። 

በቸር ያቆየን! 

ሰኔ 19 2013 ዓ ም 

Map of the 71 Irob civilians massacred in various Irobland during the first two weeks of January 2021 Eritrean army rampage. Click on the map pins for the village names and number of victims.